መልዕክት መልዕክት

Back

የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈፃሚ መልዕክት

የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን የቀድሞው ኪቤአድ ረጅም ዕድሜ ያስቆጠረና በመንግሥት ቤቶች አስተዳደር በተለይም በደርግ ጊዜ በቤት ልማት ላይ በመሳተፍ እና የተለያዩ ሥራዎችን በመሥራት አገልግሎት ሲሰጥ ቢቆይም የዕድሜውን ያህል ያላደገና ሀብት ያላፈራ ከመሆኑም በላይ በተለያዩ የተወሳሰቡ ውዝፍ ችግሮች ተተብትቦ የተቋሙ ኀልውና ከፍተኛ ሥጋት ላይ ወድቆ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ተቋሙ በዚህ አስቸጋሪ ነባራዊ ሁኔታ ውስጥ እያለ መንግሥት በየጊዜው እየጨመረ የመጣውን የቤት እጥረት ለማቃለል አጋዥ ይሆን ዘንድ ለተቋሙ ልዩ ትኩረት በመስጠት በአዲስ መልክ እንዲደራጅ በማድረግ ለ28 ዓመታት ቆሞ የነበረው የቤት ግንባታ ዳግም እንዲጀምር አዲስ ተልዕኮ ተሰጥቶታል። ከቤት አስተዳደር በተጨማሪ የቤት ልማት ላይ እንዲሰማራና ተልዕኮውንም በብቃት እንዲወጣ መንግሥት አዳዲስ አመራሮችን በመመደብ ወደ ሥራ እንዲገባም አድርጓል፡፡

በዚሁ መሠረት አዲሱ የለውጥ አመራር ባለፉት አራት ዓመታት ሀገራዊ ሪፎርሙን መነሻ በማድረግ ተቋሙን ትርጉም ባለው ደረጃ መለወጥ የሚያስችል ሁሉን አቀፍ ሪፎርም አቅዶ በመተግበር በሁሉም ዘርፎች የሚያበረታታና ተስፋ የሚሰጥ ስኬቶችን እያስመዘገበ ይገኛል፡፡ ይህ የተቋሙ ስኬት የተፀነሰው ከሀገራዊው ሪፎርም ሲሆን አመራሩ ለተቋሙ ለውጥ ቁርጠኛ በመሆኑ ያስቀመጠውን ራዕይ ዕውን ለማድረግ ያላሰለሰ ጥረት አድርጓል፡፡

ለዚህም ሪፎርሙ መሠረት ያደረገው ጠንካራ ተቋም የመገንባት ራዕይ በአጠቃላይ የተቋሙን ችግር ሊፈቱ የሚችሉ የዐቅም ግንባታ ሥራዎችን መሥራት እና ተቋማዊ የሐሳብ እና የተግባር አንድነት መፍጠር፣ የተሳለጠ የሀብት አስተዳደር ሥርዓት መዘርጋት፣ ተቋሙን ወደኋላ ሲጎትቱ የኖሩ ውዝፍ ሥራዎችን በማጠናቀቅ እና ሌላ ውዝፍ እንዳይፈጠር ማድረግ፣ እንደ ተቋም ይሁን እንደ ሀገር የሚንፀባረቀውን የቤት እጥረት መፍታት የሚያስችል የቤት ግንባታ በስፋት ማከናወን ለአብነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ እነዚህን መሠረታዊ ነጥቦች ለይቶ ሪፎርሙን ለመተግበር የተነሳው አመራር ሥራውን መልክ መልክ ለማስያዝ እንዲረዳው የዝግጅት እና የትግበራ ምዕራፎችን ለይቶ ለመንቀሳቀስ ጥረት አድርጓል፡፡

በዝግጅት ምዕራፉ የተቋሙን ችግሮች በወጉ ለይቶ የማወቅ፣ ያሉትን ዕድሎችና ሥጋቶች የመለየት፣ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮችን ተረድቶ መፍትሔዎችን የማበጀት፣ የዐቅም ግንባታ እና የግብዓት ፍላጎቶችን ካለው ዐቅም ጋር አገናዝቦ ስትራቴጂዎችን የመንደፍ፣ አመራሩን እና ፈጻሚውን የማዘጋጀት ሥራዎችን ሠርቷል፡፡ በዚህ ሂደት ተቋሙን አላላውስ ብለው የኖሩ የተዛነፉ አመለካከቶች፣ የአሠራር፣ የአደረጃጀት እና የሰው ሀብት ዐቅም ውስንነቶች፣ የፋይናንስ እጥረቶች፣ ደካማ የሀብት አስተዳደር፣ ቅንጅት የጎደለውና ደካማ የአገልግሎት አሰጣጥ እና ሌሎችም መፍትሔ የሚያሻቸው ሆነው የተለዩ ጉዳዮች ናቸው፡፡ እነዚህን እና ሌሎች ዘርፈ ብዙ ችግሮችን በዝግጅቱ ወቅት ለይቶ የተነሳው የለውጥ ሂደት ወደ ቀጣዩ የትግበራ ምዕራፍ ግልጽ አቅጣጫዎችን ይዞ መሻገር ችሏል፡፡

በመሆኑም በትግበራው ሂደት በቅድሚያ ተቋማዊ መግባባት እና የጋራ አጀንዳ ለመፍጠር የሚያስችሉ ውይይቶችን በማድረግ የኢንዱስትሪ ሰላም የሰፈነበት ተቋም ለመፍጠር ጥረት ተደርጓል፡፡ የአገልግሎት አሰጣጡን ለማሻሻል የዐቅም ግንባታ ስትራቴጂ በማዘጋጀትና ሥልጠናዎችን በመስጠት የተቋሙን ተልዕኮ መሸከም የሚችል የሰው ኃይል መፍጠር ተችሏል፡፡ በመቀጠል ለዓመታት የቆዩ የቤት አስተዳደር ችግሮች መፍታት ላይ ትኩረት ሰጥቶ በመንቀሳቀስ የሚያስተዳድራቸውን ቤቶች ቆጠራ በማካሄድ በዓይነት፣ በሚገኙበት አድራሻ፣ በተጠቃሚ ዓይነት፣ የቤቶቹን ደረጃና ተያያዥ መረጃዎችን ለይቶ በዘመናዊ መንገድ የማደራጀት፣ የኮርፖሬሽኑን የሀብት መጠን ለማወቅ በገለልተኛ አካል የማስጠናት፣ ለቤቶቹና ይዞታዎቹ የባለቤትነት ማረጋገጫ ካርታ የማውጣት ሰፊ ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የኮርፖሬሽኑን መብት እና ጥቅም በሕግ የማስከበር፣ ቤቶች እና ሕንፃዎችን የማደስ፣ የሥራ አካባቢን ምቹ ለማድረግ የዋና መሥሪያ ቤት እና ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶችን ቢሮ የማደስ እና የማስዋብ፣ አገልግሎት አሰጣጡን ለማዘመን ዘመናዊ የመረጃ ሥርዓት የመዘርጋት ወዘተ… ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡ ሌላው የሪፎርሙ ዋና ማጠንጠኛ ተደርጎ የተወሰደው በአዲስ መልክ የተሰጠውን የቤት ልማት ተልዕኮ ማሳካት ነበር፡፡

በመሆኑም ኮርፖሬሽናችን የቤት እጥረት ችግርን ለመፍታትና የሀገራችንን ቀጣይ የብልጽግና ዘመን ታሳቢ የሚያደርግ ደረጃውን የጠበቀ የቤት ልማትን ማሳካት የኅልውና ጉዳይ መሆኑን በመገንዘብ ጠንካራ የክትትልና የድጋፍ ሥርዓት በመዘርጋት እንዲሁም የተሻለ ልምድ ያለውን የፕሮጀክት አማካሪ ድርጅት በመቅጠር፣ አላስፈላጊ ቢሮክራሲን በማስወገድ፣ ከኮንትራክተሮች እና አማካሪዎች ጋር መደበኛ የሦስትዮሽ የጋራ መድረክ በመፍጠር እና ግንባታዎቹን በምዕራፍ በምዕራፍ በመከፋፈል በ10 ሳይቶች ላይ ሰፊ የቤት ልማት ሥራዎችን ተግብሯል፡፡

እስካሁን በአሥር ሳይቶች ግንባታቸው ከተጀመሩ ፕሮጀክቶች ጋር ተያይዞ ቤቶቹን ገንብቶ ለአገልግሎት ከማዋል ባለፈ በግንባታው ሂደት ውስጥ ብዙ ሌሎች ተጨማሪ ጥቅሞችን ማለትም ከፍተኛ ገንዘብ ወደ ገበያው በማስገባት ኢኮኖሚውን የማነቃቃት፣ ከአስር ሺህ በላይ ለሆኑ ሥራ አጥ ዜጎች የሥራ ዕድል የመፍጠርና ከየአካባቢው የከተማ አስተዳደር መዋቅር ጋር በመቀናጀት በግንባታው የተሣተፉ ተቋራጮች በአካባቢው ልማትና ማኅበራዊ ድጋፎች ላይ በመሳተፍ የዜግነት ግዴታቸውን በራሳቸው ፍላጎትና ተነሳሽነት እንዲወጡ በማመቻቸት ዘርፈ ብዙ ጥቅሞችን አስገኝቷል፡፡

የሪፎርም ሥራዎችን መሠረት በማድረግ በርካታ ሥራዎች የተከናወኑ መሆኑ እሙን ቢሆንም የተቋሙ ቀጣይ ሂደት ላይ እንደ ሥጋት ተጋርጦ የነበረው የፋይናንስ ጉዳይ ነበር፡፡ ኮርፖሬሽኑ እንደ አዲስ በመንግሥት የልማት ድርጅት አሠራርና አደረጃጀት እንዲቋቋምና የቤት ልማትን እንዲያከናውን ተጨማሪ ተልዕኮ በወሰደበት ወቅት የበጀት ምንጭ ተብለው ታሳቢ የተደረጉት አማራጮች ከመንግሥት፣ ከባንክ ብድርና የተቋሙን ገቢ በማሳደግ ሲሆን ወቅቱ በሀገራችን ሁለንተናዊ የሪፎርምና የሽግግር እንቅስቃሴዎች የተጀመረበትና መንግሥታችንም ባዶ ካዝና የተረከበበት ጊዜ በመሆኑ ከመንግሥት የግንባታ በጀት መጠየቅ አግባብ ባለመሆኑ እንዲሁም ከባንክ ብድር ለመጠየቅ ቢታሰብም ኮርፖሬሽኑ በዚያን ጊዜ የነበረበት ነባራዊ ሁኔታ ለ4ዐ ዓመታት የተወሳሰቡ የፋይናንስ አስተዳደር ችግሮችና አሉታዊ የኦዲት አስተያየቶች በመኖራቸው ምክንያት ብድር ለመጠየቅ የሚያስችሉ መሥፈርቶች የተጓደሉበት ሁኔታ ነበር፡፡

በመሆኑም ብቸኛው አማራጭ የተቋሙን ገቢ በማሳደግ ልማቱን መጀመር በመሆኑ በዚሁ መነሻ የተለያዩ የገቢ ማሻሻያ አማራጮችን በማጥናትና በመተግበር በፈጠርነው ሀብት በሁለት ዓመት ከጀመርናቸው አሥር ሳይቶች ውስጥ ዘጠኙን በራሳችን ገቢ እያስገነባን ሲሆን፣ መንግሥት የጀመርናቸውን ፕሮጀክቶች አፈጻጸምና የኮርፖሬሽኑን ጥረትና ተነሳሽነት ከግምት ውስጥ በማስገባት ለገርጂ አዲሱ የመኖሪያ መንደር ግንባታ በከፊል በጀት በመመደብና በከፊል ብድር በማመቻቸት የጀመርነው ስኬታማ የልማት ጉዞ ቀጣይነት እንዲኖረው ትልቅ ዐቅም እና ሞራል ፈጥሮልናል፡፡

በዚሁ አጋጣሚ ሊገለጽ የሚገባው ስለንግድ ቤት ተከራዮቻችን ነው፡፡ እነሱ ጨምረው የከፈሉት ገንዘብ እና እኛም በገባነው ቃል መሠረት ውጥናችን ፍሬ አፍርቶ ተጨማሪ የንግድ ቤቶች ተገንብተው ሌሎች ዜጎች የዕድሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ስላደረጉ ያለኝን አክብሮትና ምሥጋና ማቅረብ እፈልጋለሁ፡፡ ኮርፖሬሽናችን በእነዚህ አራት ዓመታት ተንቀሳቅሶ ያገኘውን ልምድ መነሻ በማድረግ እንደ ሀገር በተዘጋጀው መሪ ዕቅድ በሚቀጥሉት አሥር ዓመታት ከቤቶች አስተዳደር ሥራዎች ጎን ለጎን በቤት ልማት ዘርፍ የተጣለውን ግብ ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የበኩሉን ድርሻ ለመወጣት አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት እያደረገ ይገኛል፡፡

በተለይ የግንባታ ቦታዎችን የመለየት፣ የተሻለ የዲዛይን አማራጮችን የማዘጋጀት እና ከግል ባንኮች ጋር በጋራ መሥራትን ጨምሮ የተለያዩ የገንዘብ ምንጮችን በማፈላለግ የተሻለ ቴክኖሎጂና ፋይናንስ ያላቸውን የውጪ ሀገር እና የሀገር ውስጥ ተቋራጮች የሚሳተፉበት ሰፊ የቤት ልማት ሥራ ለማካሄድ ዝግጅቱን ከወዲሁ የጀመረ ሲሆን በቤት እጦት ለሚቸገሩ የከተማ ነዋሪዎች፣ የመንግሥት ሠራተኞች እና አመራሮች ቤቶችን ገንብቶ ለአገልግሎት ለማቅረብ ከትላንቱና ከዛሬው ጥረትና ድካም በላይ ነገን የበለጠ ሸክም እንዳለበት በመረዳት የተቋሙን የነገ ራዕይና ተልዕኮ ብሩህ የማድረግ ሥራ አጠናክሮ ይቀጥላል፡፡

ኮርፖሬሽናችን ያሉበትን የረጅም ዓመታት ውስብስብ ችግሮች በመፍታት በመንግሥት የተሰጠውን ተልዕኮ ከግብ ለማድረስ ባለፉት አራት ዓመታት ብዙ የሪፎርም ሥራዎችን በመተግበር የሚጨበጥና ተስፋ የሚሰጡ ጅምር ስኬቶችን ለማስመዝገብ በተንቀሳቀሰባቸው በእነዚህ ዓመታት ያጋጠሙንን ብዙ ውጣ ውረዶችና ተስፋ የሚያስቆርጡ መሰናክሎችን ልናልፍ የቻልነው ለኮርፖሬሽኑ መለወጥ መልካም አስተሳሰብ ካላቸው አካላት ጠንካራ ድጋፎች ስለተደረገልን በመሆኑ ሁሉም የኮርፖሬሸኑ አመራርና ሠራተኞች የሚያስታውሱት በጥልቅ የሚገነዘቡትና በታላቅ አክብሮት የሚያመሠግኑት መሠረታዊ ጉዳይ ነው፡፡

ከዚህ አንጻር ኮርፖሬሽኑ ዛሬ ለደረሰበት ጅምር ስኬት ከጎናችን በመሆን ጠንካራ ድጋፍና ትብብር ካደረጉልን መካከል ከባለራዕዩ የለውጥ መሪያችን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ጀምሮ የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት የሥራ ኃላፊዎች ጠንካራ የቅርብ ክትትልና ድጋፍ በማድረግ በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ፡፡ የኮርፖሬሽኑ የሥራ አመራር ቦርድ አባላትም አጠቃላይ የኮርፖሬሽኑን ሁለገብ የሪፎርም ትግበራ በቅርበት ክትትልና ድጋፍ በማድረግ ሚናቸው ከፍተኛ የነበረ ሲሆን በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት የከተማ ልማት፣ ኮንስትራክሽንና ትራንስፖርት የቀድሞው ቋሚ ኮሚቴ አባላት የኮርፖሬሽኑን ሁሉን አቀፍ ሪፎርም በቅርበት በመገምገምና ወደ መሬት ወርዶ በማየት አበረታች ግብረ መልስና ድጋፍ በመስጠት ድርሻቸውን በሚገባ ተወጥተዋል፡፡

እንዲሁም የኢፌድሪ ገንዘብ ሚኒስቴር ለገርጂ ፕሮጀክት ትግበራ የፋይናንስ ድጋፍ በመስጠትና ብድር በማመቻቸት፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ለፕሮጀክቶች የማጠናቀቂያ ግብዓቶች ግዢ የሚያስፈልገውን የውጭ ምንዛሪ በመፍቀድ፣ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለገርጂ ፕሮጀክት የፋይናንስ ብድር በመስጠት፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በግንባታ ፈቃድ አሰጣጥ፣ የመሠረት ልማት አቅርቦትና ሌሎችም ሰፊ ድጋፎችን በመስጠት አሻራቸውን አኑረዋል፡፡

በመጨረሻም የኮርፖሬሽናችን የሥራ መሪዎችና ሠራተኞች እንዲሁም የሠራተኛ ማኅበር አመራሮች የኢንዱስትሪ ሠላም ሰፍኖ የተግባርና የአስተሳሰብ አንድነት ፈጥራችሁ እንደ ሀገር የተጀመረውን ሁለንተናዊ ኢትዮጵያን የማሻገር ሪፎርም ተቀብላችሁ በመተግበር የተገኘውን ውጤት ላስመዘገባችሁና በቀጣይም የበለጠ ውጤት ለማስመዝገብ ቃል የገባችሁ በጣም ከፍ ያለ ምሥጋና እያቀረብኩ ይህ ጥረታችሁ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ከአደራ ጭምር እጠይቃለሁ፡፡

አመሰግናለሁ!!

አቶ ረሻድ ከማል

የፌደራል ቤቶች ኮርፖሬሽን

ዋና ሥራ አስፈጻሚ

2015 ዓ.ም


የፌ.ቤ.ኮ ሜይል የፌ.ቤ.ኮ ሜይል

ይከተሉን ይከተሉን

ተዛማጅ ገጾች ተዛማጅ ገጾች