ዜና ፌ.ቤ.ኮ
ኮርፖሬሽኑ እና የሠነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት በመረጃ ልውውጥና በሠነድ ማረጋገጥ በትብብር ለመስራት ተስማሙ

የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን እና የሠነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ አገልግሎት በመረጃ ልውውጥና በሠነድ ማረጋገጥ ሥራን በትብብር ለመስራት ስምምነት ደርሰዋል፡፡
በስምምነቱ መሰረት ከደንበኞች የሚቀረቡትን የሰነድ ማስረጃዎች ትክክለኛነት ለማረጋገጥ የሠነዶች ማረጋጋጫ ሲሰተምን ከኮርፖሬሽኑ ሲስተም ጋር በማስተሳሰር የኮርፖሬሽኑ ባለሙያዎች አገልግሎት ሲሰጡ በቀላሉ ማረጋገጥ የሚያስችል እንደሆነ ተገልጿል፡፡
ስምምነቱን የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ክቡር አቶ ረሻድ ከማልና የሠነዶች ማረጋጋጫና ምዝገባ አግልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ደጋቶ ኩምቤ በዛሬው እለት ፈርመዋል፡፡
ስምምነቱ የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን የመንግስትና የሕዝብ የሆኑ ሀብቶችን ከሕገወጦች ለመከላከል እያደረገ ያለውን ውጤታማ እንቅስቃሴ ስኬታማ እንዲሆን የላቀ ድርሻ እንደሚኖረው የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ክቡር አቶ ረሻድ ከማል ተናግረዋል፡፡
ኮርፖሬሽኑ የሚያቀርበውን አገልግሎት ጥራት ለመጨመርና ቀልጠፋና ዘመናዊ አገልግሎት ለደንበኞቹ ለማቅረብ ከወሳኝ አካላት ጋር አሰራሩን ሙሉ በሙሉ ዲጂታላይዝ በማድረግ በቴክኖሎጂ እያስተሳሰረ እንደሆነም ገልፀዋል ፡፡ የዛሬው ስምምነትም ተቋሙ ዲጂታል አገልግሎት ለማቅረብ ከሚያደርጋቸው በርካታ ተግባራት መካከል ውስጥ አንዱ ነው ብልዋል ዋና ሥራ አስፈጻሚው፡፡
የሰነዶች ማረጋጋጫና ምዝገባ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ደጋቶ ኩምቤ በበኩላቸው የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በከፍተኛ ለውጥ ያለ ተቋም መሆኑን አውስተው ስምምነቱ የኮርፖሬሽኑ ደንበኞች የሚያቀርቡትን ሠነዶች ትክክለኝነት በቀጥታ በተዘረጋው ሲስተም መሰረት ኮርፖሬሽኑ ማረጋገጥና ዋናውን የሰነድ ቅጅ ከሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ማግኘት የሚያስችለው እንደሆነም ነው የገለጹት፡፡
ይህም ከውክልና እና ከመልካም ስም ሽያጭ ጋር የተያያዙ ሥራዎችና ከሌሎች አገልግሎቶች ጋር ተያይዞ የሚቀርቡ ሠነዶችን ትክክለኛነት በቀላሉ ማረጋገጥ የሚያስችለው እንደሆነ ነው ዋና ዳይሬክተሩ የገለጹት፡፡