ዜና ፌ.ቤ.ኮ
የአዘርባጃን የቤት ልማት ኤጂንሲ እና የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በቤት ልማት ዙሪያ በጋራ ለመስራት በሚያስችላቸው ጉዳዮች ላይ ስምምነት ደረሱ
በክቡር ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ የተመራው እና የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ክቡር አቶ ረሻድ ከማልን ያካተተው ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች የልዑካን ቡድን በቤት ልማት ዙሪያ ባካሄደው ምክክር የአዘርባጃን የቤት ልማት ኤጂንሲ እና የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን በጋራ ለመስራት በአዘርባጃን ዋና ከተማ ባኩ ስምምነት ላይ ደርሰዋል ፡፡
የልዑካን ቡድኑ አባል የሆኑት ፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ክቡር አቶ ረሻድ ከማል አቻ ከሆነው ተቋም ከአዘርባጃን የቤት ልማት ኤጂንሲ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ጋር ሰፊ ምክክርና ውይይት አድርገዋል፡፡
የአዘርባጃን የቤት ልማት ኤጂንሲ በመንግስት መነሻ የኢንቨስትመንት ፋይናንስ ድጋፍ ተደርጎለት የሚገነባቸውን ቤቶች ከ 30 በመቶ እስከ 40 በመቶ ከገበያው የዋጋ ቅናሽ ያላቸውን ቤቶች ለአገሪቱ ዜጎች በሽያጭ እያቀረበ ገበያ የማረጋጋት ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝም ተጠቅሷል፡፡
የአዘርባጃን የቤት ልማት ኤጂንሲ ከመንግስት የሚያገኘውን መነሻ የኢንቨስትመንት ፋይናንስ ድጋፍ ሙሉ በሙሉ ገበያ ለመረጋጋት ለሚገነባቸው ቤቶች ግንባታ የሚያውል ሲሆን ያገኘውን የበጀት ድጋፍ ለመንግስት የመመለስ ግዴታ የሌለበት ተቋም እንደሆነም ተጠቁሟል፡፡
የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሪል ስቴት ገበያውን ለማረጋጋት እያደረገ ላለው ጥረት የአዘርባጃን የቤት ልማት ኤጂንሲ ያለውን ሰፊ ልምድ ለፌዴራል ቤቶች የሚያጋራ ይሆናል፡፡
ሁለቱ ተቋማት በቤት ልማት ዙሪያ በትብብር ለመስራት በሚያስችላቸውን ጉዳዮች ላይ ስምምነት በመደረሱ የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን የአዘርባጃን የቤት ልማት ኤጂንሲን ልምድና ተሞክሮ በኢትዮጵያ ተግባራዊ ለማድረግ እንደሚሰራም ታውቋል፡፡
የቀድሞው ኪራይ ቤቶች የአሁኑ የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ራሱን ጠንካራ መንግስታዊ የሪል ስቴት ካምፓኒ ለመሆን በሚያስችለው አግባብ እየደረጀ ሲሆን የሪል ስቴት ገበያው እንዲረጋጋ የራሱን ሚና እየተጫወተ ነው።